Monday, May 8, 2017

Ethiopia Media Development



ፌስቡክ ሚያዚያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም
ኢህአዴግና መጪው የአካል ጉዳተኝነት አደጋ[ ከሰላምወርቅ ሁሉ አገር]
ክፍል ሶስት
ሚድያ ፣ ህዝብና አገር፤ ይቅርታ ይደረግልኝና ዛሬም ሚድያውን መውቀሴ አልቀረም።ሚድያ ከቴክኖሎጂ ማደግና ከግሎባላይዜሽ ጋር ተያይዞ በአንድ ሰውና በአንድ ቤት የተደረገ ነገር በአንድ ሴኮንድ በመላው አለም የመዳረስ አቅም አግኝቷል።ሚድያ በርካታ ተልእኮ እንዳለው ሲነገር እኔም እንደ እናንተ ሰምቻለሁ።ከነዚህ ውስጥ የአንድ የኢኮኖሚ ስርአት ማገልገል፣ ማዝናናትና ማሳወቅ ወ.ዘ.ተ ይባሉ እንጂ ዞሮ ዞሮ በሁሉም መስክ ተፅእኖ ማሳደር የሚለው ዋነኛ እንደሆነ ክርክር የለውም።በዚህ ረገድ በአለም የተከሰቱ የቀለም አብዮቶች፣ጦርነቶችና ግጭቶች የሚድያ ድርሻ በጣም ከፍተኛና ወሳኝ እንደነበር ከሩቅ እስከ ቅርብ የነበሩ ታሪኮችና ሁኔታዎች ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል። በቬትናምና አሜሪካ ጦርነት ወቅት፣በቅረቡ በግብፅ የተካሄዱ የመንግስት ለውጦች፣ሁሉም የቀለም አብዮቶች በመሳሰሉ ሚድያዎች የነበራቸው ድርሻ መተክያ እንዳልነበረው ማየት ይቻላል።
ሚድያ የአንድን አገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያሰቀይራል።በአገራት መካከል ያለን ግንኙነት ያሻሽላል ያበላሻል።በአጠቃላይ ሚድያ የአንድ አገር ህዝብ አስተሳሰብ ወደ ሚፈልገው መንገድ በመዘወር በሌላው ህዝብ፣በራሱ መንግስት እንዲሁም በአለም አቀፍ ሁኔታ የጥፋት ወይም የድጋፍ አስተሳሰብና እርምጃ እንዲወስድ የማድረግ አቅም አለው።ይህ ከሆነ ዘንዳ ሚድያ አይደለም አንድ አገር አለምን የመቀየር አቅም አለው። በቅርቡ በቱርክ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከተካሄደ በኃላ የቱርክ ሚድያዎች በመፈንቅለ መንግስቱ ጀርባ አሜሪካ እጇ አለበት በሚል መዘገባቸው ብቻ በወቅቱ 75% የቱርክ ህዝብ ፀረ አሜሪካ አቋም መያዙ በወቅቱ የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት ያስረዳል።የእንግሊዝ ህዝብ አገሩ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት እንዳለባት ሲወስን ሚድያ ትልቁ ድርሻ እንደተጫወተ ተደጋግሞ ሲነገር ሰምቻሎህ።አሌክሳንደር ቤስት የተባለ የሶሻል ሳይንስ ሙሁር TED በሚባል የሃሳብ መንሸራሸርያ ሚድያ why brexit happened and what to do next በሚል ሚድያው ላይ ቀርቦ በገለፀው ሃሳብ እነዚህ ከአውሮፓ ህብረት እንውጣ ብለው ድምፅ የሰጡ አከባቢዎች ከሕብረቱ ይበልጥ ተጠቃሚ ነበሩ ብሎ ሚድያው ተጠቃሚነታቸው ሳይገልፅ መለየታቸው እንደሚጠቅማቸው በመቀስቀሱ ፀረ-ጥቅማቸው ድምፅ እንዲሰጡ ማድረጉ ይገልፃል። የአገሪቱ ህዝብ ተጠቃሚነቱ የሚፃረር አስደንጋጭ ውሳኔ ከወሰነ በኃላ አንዱ ጠ/ ሚኒስትሩ ህዝበ ዉሳኔ በመጥራቱ ተጠያቂ ሲያደርግ ሌላው ለተማረው ክፍል፣ የተማራው ላልተማረው በመወንጀል ተጠያቂ ማድረግ ጀምረዋል ይላል።
በአሁኑ የአሜሪካ ምርጫ ሄላሪ ክሊንተን ከተመራጩ ፕሬዝዳንት የተሻሉ ነበሩ የሚል የብዙ የአለም ክፍል አስተያየት ነው።በተወካይ ተወካይ ሳይሆን በህዝብ ምርጫ ክሊንተን ከሁለት ሚልዮን ድምፅ በላይ ትራምፕን በልጠው እንደነበር እንደተጠበቀ ሆኖ በዴሞክራቶች መካከል በነበረ ምርጫ አቶ አንደርሰን ከክሊነቶን የተሻለ ለአብዛኛውና ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅም የምርጫ አጀንዳ ነበራቸው።ሚድያው በተጫወተው ሚና ግን እኛ 99% አሜሪካውያን በ1% እየተጎዳን ነን ያለው አሜሪካዊ ለድሃው የተሻሉ የተባሉ ተመራጭ ጥሎ ሄላሪን ወከለ። እንዲህ እያልን ብዙ ምሳሌዎች ማቅረብ ይቻል ይሆናል።ከዚህ ብቻ መረዳት የሚቻለው ሚድያ የዳበረ አስተሳሰብ አለው ለሚባል ማህበረሰብም ጭምር ተፅእኖ ፈጥሮ ፀረ ተጠቃሚነቱ ማሰለፍ ይችላል ነው።
ወደ ራሳችን ቤት ወደ አገራችን እንመለስና ሚድያው ለዚህ አገር አንድነት፣ ሰላም፣ዴሞክራሲና ልማት እያበረከተው ያለ አስተዋፅኦ በሚፈለገውና በሚገባው ደረጃ አይደለም የሚል እምነት አለኝ።ይህ ሲባል ምንም አልሰሩም እያልኩ እንዳልሆነ ግን ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባልኝ እፈልጋለሁ። ለምሳሌ ከመጀመርያው ተሃድሶ በኃላ ድህነት ከምንም በላይ ጠላታችን እንደሆነ፣በሚሌንየም አከባቢ ውጭ የሚገኘው ዳያስፖራ ወደ አገሩ ገብቶ በልማት ተሳታፊ እንዲሆንና በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ መሆናችን፣ ገፅታችን እየተቀየረ መሆኑ በመሳሰሉት የተሰራ ስራ አለ።ለዚህም ተገቢው ዋጋ እሰጣለሁ።ይህ ግን በዋናነት በመንግስት ሚድያዎችና የተወሰኑ ኃላፊነት አለብን ያሉ የግል ሚድያዎች የታጠረ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል።በቁጥር አንድ ወይም ሁለት ከሚባሉት የግል ሚድያዎች በስተቀር አንዳንዶቹ ጭራሽ የተሰራ በጎ ስር እንዳይታየን መጋረጃ ሲፈልጉ፣አንዳንዶቹ ሰላም ልማትና ዴሞክራሲ የሚባሉ ቃላቶች ኢህአዴግ የፈጠራቸው ስለሚመስላቸው እነዚህን ቃላት አንስቶ መፃፍ ወይም መናገር ገለልተኛ አልባልም ብሎ የሚያስብና አንዳንዱ ደግሞ በነፃ ፕረስ ስም ከፖለቲካዊ አቋሙ አንፃር ሆን ብሎ አጣሞ ለህዝብ በማቅረብ ህዝቡ የተሳሳተ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ወገቡ ታጥቆ ይሰራል።እንደኔ ትእዝብት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የአቅም ውስንነት፣የልምድ እጥረት፣የፖለቲካ መሳርያ አድርጎ መጠቀም በመሳሰሉ ጉዳዮች የተተበተበ ነው።በቅርቡ እሁድ ጧት በሸገር ሬድዮ በሚድያ ዙርያ በነበረ ጠቃሚ ውይይት ተወያዮቹ በችግሩና በችግሩ ምንጭ ዙርያ ጠቃሚ ሃሳቦች አንስቷል።በተለይ ከፎርቹን ጋዜጣ ይቀርብ የነበረ ሃሳብ ድጋፍ አለኝ። አንዳንድ ጋዜጠኞች በሌላው ማህበረሰብ ያለው የልምድ፣አባባል፣የታሪክና የባህል ሁኔታ ምንም ግንዛቤ እንኳን ሳይኖራቸው አለምን የሚያዳርስ የሬድዮ ወይም የቴሌቭዥን መነጋገርያ በእጃቸው እንዲጨብጡ በማድረግ ግራ ገብቷቸው ግራ ያጋባሉ።አንድ የFM 97.1 ጋዜጠኛ “በተለምዶ የአክሱም ሃወልት እየተባሉ የሚጠሩ በአክሱም የሚገኙ ሃወልቶች” ብሎ አቅርቧል። ስለ ስምና የተለምዶ ስም ልዩነት ማን ይንገርልኝ።ይህ ስም ማጥፋት ነው ካላቹ የ17/12/2008 ዓ/ም ፕሮግራማቹ ፈትሹ።ርእስ መረጣና ዝርዝሩ የተዛባ መልእክት ማስተላለፍ ብዙ ነው። በ13/01/2009 ዓ/ም የሸገር የቀትር ወሬ ላይ መንግስት የአ/አበባ የቤት ችግር በኮንዶምንየም አልፈታም አለ ይላል።ኮንደምንየም መስራት አቆመ ብየ ዝርዝሩ ጠብቄ ስሰማ ከኮንዶምንየም በተጨማሪ ሌሎች አማራጮችንም መፈለግ እንደሆነ ተረዳሁኝ። ብዙ ግዜ የሚገርመኝ አንድ የግል ተብሎ የተሰየመ ሚድያ የግል የሚባለውና ገለልተኛ መሆኑ የሚረጋገጠው ስለ መንግስት ጥሩና ድክመቱ ሰብሰብ አድርጎ በመጥፎ የሚፅፍና የሚናገር እንደሆነ የሚያስብ፣ ሚድያ ሚድያ የሚባለው ስለ ሰላም ሳይሆን ስለ ጦርነት ሲዘግብ እንደሆነ፣ምልአተ ህዝቡ ሰላም ሆኖ ከታያቸው በህዝቡ ውስጥ የሁለት ጎረቤታሞች ግጭት እንዴት ወደ ህዝብ ለህዝብ ግጭት ተሸጋግሮ ለዜና እንዲበቃ መደረግ እንዳለበት መፀለይና መጓጓት የሚድያ ግብ አድርጎ የሚያስብ አስተሳሰብ መንገሱ ነው።የአገሬ የሚድያ ማህበረስ ሆይ! አገራችን በማህበራዊ ሚድያ የተዛቡ መልእክቶችና ቅስቀሳዎች ገብታበት የነበረ የጨለማ ጉዞ አይታቹሃል። የሌላ አለም ተሞክሮም ብዙ ነው።በሚድያ ስራ በርካታ አገሮች ፈርሰዋል።ምናልባት ግን እነዚህ አገሮች በሽግግር መንግስት ወይም በጥምር መንግስት ወዘተ ተመልሰው አገር የመሆን አጋጣሚ ሊያገኙ ይችሉ ይሆናል።እኛ ይህንን አጋጣሚ ደግመን የማግኘት እድላችን ወደ ዜሮ የተጠጋ እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ወይም የፖለቲካ ፍላስፋ መሆን ሳይጠይቅ በተለያየ ቁርሾ የተሞላ የመጣንበት ታሪካችንና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ታሪካዊ ጠላቶቻችን እንዲፋፋም በማድረጋቸው ወዴት አምርቶ እንደነበር ማየት መቻላችን በቂ ነበር።ስለሆነም እባካቹ ይህችን አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታቹ ተወጡ።
ወቅታዊ አለማቀፋዊ ሁኔታና የውጭ ግንኙነታችን፤ ከቀዝቃዛ ጦርነት ማብቃት በኃላ አለም በአንድ የመሀል ዳኛ ብቻ ፍርድ ትቀበል እንደነበረ ሁላችን የምናውቀው ጉዳይ ነበር።ብዙ ሊቃውንት ብለን የምንላቸው ፀሐፍትና የመስኩ ተኝታኝ የሚባሉ ሰዎች ይህ የአንድ የአለም ዳኛና ከሱ ጋር ተያይዞ ያለው አዲሱ ሊበራሊዝም{Nio-liberalism} የአለም ሁሉ አስተሳሰብና መመርያ ሆኖ የሚቀጥልና ምናልባትም እስከወድያኛው የሚተካው አስተሳሰብ አይኖርም ያሉ ብዙ ናቸው።በተነፃፃሪ ብዙ አልቆየም በሚባል ወቅት የዚህ አስተሳሰብ መሸርሸርና አለም ከአንድ አድራጊ ፈጣሪ ወጥታ በቀዝቃዛው ጦርነት ከነበሩት ሁለት አለቆች በላይ ወደ ብዙ ጉልበተኛና አንዱ የአንዱ ተፅእኖ ለመቋቋም ሲል የቻለውን ሁሉ ማድረግ የጀመረበት ሁኔታ እንዳለ እያየን እንገኛለን።ኒዮ ሊበራሊስቶች የአለም መጨረሻ ያሉትን አስተሳሰብ በተግባር መሸርሸር የጀመሩት ራሳቸው ናቸው።ኒዮ ሊበራሊዝም አንድ ድንገተኛ ጎርፍ እንኳ መከላከል የማይችል መሆኑ ተጨባጭ ማሳያ የሆነው እ.አ.አ 2008 ያጋጠመ የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የዚህ አስተሳሰብ ባለቤት የተባሉና ሌሎች አገሮች “በውድም በግድም በዚህ መጓዝ አለባቹ ካልሆነ የተረጋጋ መንግስት ሁናቹ መቀጠል አትችሉም” እያሉ ዱላ ሲመዙ በሌላ በኩል ራሳቸው የአስተሳሰቡ ባለቤቶች የጨዋታው ህግጋት ሲጥሱት ታይቷል። ባንኮቻቸው ሲከስሩ፣ካንፓኒዎቻቸው ሲንገዳገዱና በአንዳንዶቹ በግብርና የተሰማሩ ዜጎቻቸው ከመንገድ እየወጡ መሆናቸው ሲያዩ በጠራራ ፀሐይ የወሰዱት እርምጃ አይተናል ሰምተናል። የሚገርመው ነገር እነሱ በቸገራቸው ግዜ እጃቸው እንኳን ሳይታጠቡ ወደ ገበያው መአድ እንዴት እንደገቡ ግልፅ ሆኖ ሳለ አሁንም በዚሁ አስተሳሰብ አንሄድም ለሚሉ አገሮች እንቀጣለን ማለታቸውና እየቀጡ መሆናቸው ነው።አገራችን የውስጥ ተጋላጭነቷ እንደተጠበቀ ሆኖ በተደጋጋሚ ፈተና ውስጥ እየወደቀች ያለችዉም በዚህ አለማዊ የጦርነት ሜዳ ላይ ነው።እስካሁን በጥናትና በመርህ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ በመከተል፣ በተነፃፃሪ ጠንካራ መንግስት ስላለንና በኢኮኖሚ ትክሻችን በማወፈር ይህንን ተቋቁመን ልክ ከ121 አመታት በፊት በምኒሊክ አመራር በህዝቦች የጋራ ቆራጥነት ፈረንጅን አሸንፈን በጭቆና ለነበሩ የአለም አገሮች ምሳሌ እንደሆነው በዚህ ዙርያም ለሌላው አለም በተለይ ለአፍሪካ አገሮች እንደ ሞዴል ሆነን ወጥተናል። ከአሁን በኃላስ?
ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአለም ፖለቲካ እየታዩ ያሉ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ለትንበያ የሚያዳግቱ መሆናቸው እሙን ነው።የቅርብ አመታት ብቻ እንኳን ብንወስድ በርካታ አስገራሚ ነገሮች ስናይ ከርመናል።እነዚህ ሁኔታዎች አንድ ባልደረባየ በአንድ የኮሌጅ መመረቅያ መፅሔት ውስጥ የመጨረሻ ቃል {last word} እየተባለ በሚጠራ ሀሳብ መስጫ ቦታ አንድ ተማሪ አሰፈረው ብሎ የነገረኝ ፅሁፍ ትዝ አስባለኝ።ተማሪው “በማህበረ-ፖለቲካ 1+1=2 የሚባል የለም ይላል አለኝ።” የዚህ ሀሳብ ስሜት ምን እንደሆነ ማብራራት አይጠበቅብኝም።ዋናው ነገር አለማቀፍ ግንኙነትም የራሱ የሒሳብ ስሌት አለውና ይሆናል ብየ ስጠብቃቸው የነበሩ ፍፃሜያቸው ያስገረሙኝ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ብጠቅስ የግብፅ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትና የአለም ማህበረሰብ ከዝምታ እስከተለሳለሰ አቋም፣ብራዚል በደቡብ አሜሪካ የአለም አንድ ሌላ ዋልታ ማእከል እየሆነች ነው በተባለበት ሁኔታ ወደ ፖለቲካ ቀውስ መግባት፣በተባበሩት መንግስታት ፍቃድና ያለ ፍቃድ የመንን ጨምሮ አገሮች በተናጠልና በህብረት ሌሎች አገሮችን የማጥፋትና የሌላው ዝምታ፣እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ውሳኔ፣ የራሻና ቱርክ ማታ ጦር ሲማዘዙ አምሽቶ ጧት የቀለጠ ፍቅር ውስጥ መግባት፣ የኮሎምብያ መንግስት ፋርክ ከሚባል አማፂ ቡድን ጋር ያደረገው የሰላም ስምምነት ህዝቡ በህዝበ ውሳኔ ውድቅ ማድረጉና የትራምፕ ምርጫ ወ.ዘ.ተ ከብዙዎቻችን ግምት ውጭ ይሆናሉ ሳይባሉ ሆኖው ከተገኙ ክስተቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ምርጫዎች የቀኝ አክራሪ አስተሳሰብ የበላይነት እያገኘ መሄድ ሳስብ በአገራችን በአንድ ወቅት የነበረ የጫማ ማስታወቅያ ትዝ አስባለኝ “ማምለጥ ነው ለጫማው በኃላ ይታሰብበታል” ይላል።ቅድምያ ለራሴ ሌላው የራሱ ጉዳይ የሚል አስተሳሰብ እነሱ በበላይነት እናቀነቅነዋለን ከሚሉት ዴሞክራሲም ሆነ ከሰብአዊነት በሚጣረስ መልኩ የፍፁም ግለኝነት አስተሳሰብ እየተራመደ ይገኛል።ከመራመድ አልፎም ወደ አሸናፊነት መምጣት ጀምሯል።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፀረ-እስልምና፣ፀረ-ጥቁር ህዝብ፣ ፀረ-ሴቶች፣ ፀረ-አለማቀፍ ትብብርና ግንኙነት፣ፀረ-ስደተኛ አቋም በግልፅ እያራመዱና ከአሜሪካ ታሪካዊ ጠላት ከምትባለው ሩስያ ጋር የጠበቀ የቢዝነስ ትስስር አላቸው እየተባሉ ባሉበት እንዲሁም ባደጉት አገራት በተለይ በአሜሪካ እንደ አስነዋሪ ተግባር የሚታይ በሰነድ የተደገፈ ግብር ያጭበረበሩ ሰው ቅድምያ ለአሜሪካ ሌላው የራሱ ጉዳይ የሚል መፎክር በማንሳታቸው ብቻ ለስልጣን በቅቷል።ይህ አለማዊ ሁኔታ ለኛ ያለው እንድምታ ምንድነው? ከቀጠናዊ ጉዳዮች አንፃር ካየንም የገልፍ አገሮች በየመን ምክንያት በሞት አፋፍ የነበረው የኤርትራ መንግስት በመደገፍ ህይወት እንዲዘራ መቻሉ፣የግብፅ መንግስት በዲፕሎማሲና መልካም ግንኙነት ድንኳን ተከልሎ ኢትዮጵያን ለመቅበር መሰረተ ሰፊ ጉድጓድ እየቆፈረ መሆኑ፣የሶማልያ ጉዳይ ብዙም የጎላ መሻሻል ሳያሳይ መቀጠሉና በከባድ ድርቅ መጠቃት የነበረውን የፖሊቲካና ፀጥታ ሁኔታ በአሉታዊ መንገድ ሊጎዳው የሚችልበት እድል እየሰፋ መሆኑ፣የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ከመጥፎ ወደ በጣም መጥፎ እያደገ ልክ እንደ ውስጣዊ ጉዳያችን እኛን ልያቃጥለን የጀመረ መሆኑ፣ሁላችን እንደምናውቀው የሱዳን ጉዳይ ጫፉ የታጣ ውስብስብ ያለ ገመድ መሆኑ፣በቅርቡ ከሪፖርተር ጋዜጣ እንዳየነው የሱማሌላንድ ወደቦች የባለ ብር አረብ አገሮች ትኩረት ከመሳብ አልፎ በአፍንጫችን መጥተው ስምምነት እስከ መፈራረም መድረሳቸው፣ ከቅርብ አመታት ወዲህ የኬንያ የፖለቲካና የፀጥታ ሁኔታ እየተወሳሰበ መምጣቱ እንዲሁም ሌሎች የአከባቢ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር የቀጠናው የበላይነት ፍኩክር ውስጥ ገብተው ግስጋሴዋ ያልወደዱላት አገሮች መኖራቸውና የውስጥ ተጋላጭነታችን እየሰፋ እንጂ እየጠበበ ያለመሆኑ ተደማምሮ ለአገራችን ከቅርብና ከሩቅ ግዜ አንፃር እንድምታው ምንድነው? ይህንን የዲፕሎማሲ ግንባር እንዲሸፍን የተመደበው የውጭ ጉዳይ ሰራዊት በምን ሁኔታ ይገኛል? ብየ ስጠይቅ ምቾት አይሰማኝም።የመጀመርያው ሀሳቤ በውጭ ጉዳይ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ተቋም አልተገነባም የሚል እምነት እንድይዝ የሚያስገድዱኝ ሁኔታዎች ስላሉ ነው።የአሰራር ማሻሻያ ጥናት BPR ያለ አግባብና ያለ ማሻሻያው አላማ ለራሳቸው ለሰዎቹ ጥቅም አስቦ የተጠናና የተተገበረ መስራቤት አለ ከተባለ አንዱ ውጭ ጉዳይ ነው የሚል እምነት አለኝ።ዲፕሎማትነት የተከበረ ሞያና አገራዊ ፋይዳውም ከፍ ያለ ሆኖ ሳለ በአሁኑ ወቅት የሞያው ብቃትና ክብር የሚያሟሉ እንዲሁም ለቦታው የሚመጥኑ አምባሳደሮች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ አምባሳደርነት ማለት የተሸጋሸጉ አመራሮች ማረፍያ፣ያኮረፉ አመራሮች ማስተንፈሻ፣ የአመለካከት ችግር አለባቸው ተብለው የተጠረጠሩ ማስረጃ የታጣባቸው አመራሮች መጠግያ እንዲሁም ከሞያው ብቃት ውጭ የብሄራዊ ተዋፅኦ መርህ መተግበርያ ሆኖ ይታያል።ከብዙ ሰዎች እንደሚሰማው ከድሀው ህዝብ ግብር ተሰብስቦ ዶላር የሚከፈላቸው ብዙ ዲፕሎማቶች ህዝቡን ለማገልገል ካላቸው ጉጉት ይልቅ ቤተሰቦቻቸው ወደ ውጭ ወስደው እዛው ለማስቀረት ያላቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው ተብሏል።በርካታ ዲፕሎማቶች ወደ አገር የሚመለሱም ቢሆን አገራዊ ስሜት ኑሯቸው ሳይሆን ከቀረፅ ነፃ መብት ተጠቅመው ተጨማሪ ጥቅም ለማጋበስ እንጂ የመመለስ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ጥቂቶች ናቸው ይባላል። የህዝብና የመንግስት ዶላር እየበሉ በፅንፈኛ ዳያስፖራ የፖለቲካ አክራሪነት ተፅእኖ ውስጥ ገብተው ፀረ-መንግስትና ህዝብ የሚንቀሳቀሱም ቁጥራቸው ቀላል አይደለም ተብሏል። ከሁሉም በላይ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ውጭ ጉዳይ የሚጓዝበት መንገድ ለየቅል የሆኑበት አጋጣሚም አያሎህ። በፖሊሲው የተቀመጠ አንደኛው መርህ ሁሉም የዲፕሎማሲ ጦር የሚያነጣጥረው ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ጉዳይና ለኢኮኖሚ እንዲሁም ከውጭ ብሔራዊ ጥቅማችን ከማስጠበቅ አንፃር ለጎረቤቶቻችን መሆን አለበት ይላል።ከዚህ አንፃር ፖሊሲው ለመተግበር የስምሪት ማእከላት፣ብቃትና ልምድ ያለው የሰው ኃይል የት መመደብ እንዳለት የሚያመላክት ሲሆን ትግበራው ስናየው የትየ ለልየ ነው።በአንዳንድ አገሮች ያለን ስምሪት በምናይበት ወቅት ለሚሾመው አምባሳደር ታስቦ ብቻ የተወሰነ ይመስላል።
ይህ የመስራቤቱ ችግር በመሀል የተከሰተ ሳይሆን ከመጀመርያው ጀምሮ እያደገ የመጣ ብልሽት አሰራርና አመራር ሲሆን በዚህ ተቋማዊ ሁኔታና አለማቀፋዊ ሁኔታ አገራዊ ጥቅምን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል አስቡት።ስለሆነም አዲሱ ሚንስትር የሚችሉ ከሆነ መጀመርያ ራስዎን ከማንኛውም አመለካከትና ችግር ፀድተው ስራዎን ተቋማዊ ለውጥ በማምጣትና ካለንበት አለማዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም አሰራር መከተልና አመራር መስጠት ግድ የሚላቸው ይመስለኛል


የፕሬስ እና መገናኛ ብዙሃን ነፃነትን በተመለከተ የኢትዮጵያ የህግ ማህቀፍ


የፕሬስ እና መገናኛ ብዙሃን ነፃነትን በተመለከተ  የኢትዮጵያ የህግ ማህቀፍ

                          ለንቃተ ህግ ስልጠና የተዘጋጀ
                                በሰላማዊት ተሰማ
  የህግ ጥናት፣መርቀቅና ማስረፅ ዳይሬክቶሬት
                              የፌ/ዐ/ሕግ
ፍትህ ሚኒስቴር
             የካቲት 2007

      መግቢያ
የፕሬስ ነፃነት ማለት ሀሳብን በተለያየ የመገናኛ ብዙሀን ማለትም በኤለሌክትሮኒክስ እና የህትመት ሚዲያዎች የመግለፅ መብት ማለት ሲሆን ይህ መብት መረጃን ጠይቆ የማግኘት እና ይህን መረጃ በተፈለገው መንገድ የማሰራጨት መብትንም ያጠቃልላል። በአብዛኛው ይህን መብት ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ውጪ የመተግበር ፍላጎት ቢኖርም ለተለያዩ አላማዎች ሲባል ይህ ነፃነት ህገ መንግስታዊ እና ህጋዊ ጥበቃዎች እየተበጁለት የሚተገበር ነው።

የፕሬስ እና ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ያለውን ታሪክ ስንመለከት በሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ተሻሽሎ የወጣው የ1948ቱ ህገ መንግስት ይህን መብት ከማረጋገጥ አኳያ ፈር ቀዳጅ የነበረ ሲሆን በዚህ ህገ መንግሠስት አንቀፅ 41 ስር "በመላው የንጉሰ ነገስት ግዛት ውስጥ በህገ መሰረት የንግግር እና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው።" በሚል ተደንግጓል።በተመሳሳይ የኤርትራ ህገ መንግስት በአንቀፅ 12/d/ ስር ሀሳብን በነፃ የመግለጽ መብት በህገ መንግስቱ የተረጋገጠ መሆኑን እና የፌደራል መንግስት ይህን መብት የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

የንጉሱ ስርአት ካበቃ በኣላ ወደ ስልጣን የመጣው የደርግ መንግስት በአብዛኛው የስልጣን ዘመኑን የፕሬስ ነፃነትን የሚያስከብር የህግ ስርአት ያልዘረጋ ሲሆን ሆኖም መስከረም 1 1980 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አዋጅ በአንቀፅ 47/1/ ስር ኢትዮጵያዊያን የንግግር፣ የፅሁፍ፣ የመሰብሰብ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

ከላይ የተገለፀው ለፕሬስ ነፃነት የተሰጡ ህጋዊ ከለላዎች ባለፉት ስርዓቶች ምን ይመስሉ እንደነበር ሲሆን በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሀንን በተመለከተ የነበረውን ተጨባጭ ታሪካዊ ዳራን ስንመለከት አጀማመሩ ከህትመት ሚዲያው ጋር የሚገናኝ ሲሆን ከቀዳሚዎቹ የህትመት ውጤቶች መሀከል በአፄ ሚኒሊክ ዘመን ይሰራጭ የነበረው አእምሮ እና ጎህ ጋዜጣዎች ተጠቃሽ ናቸው። በተለይ በአፄ ሀይለስላሴ ዘመን በቁጥር በርከት ያሉ ጋዜጣዎች ይታተሙ የነበረ ሲሆን ከነዚህም መካከል የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ ሰንደቅ አላማችን፣ ህብረት፣ አዲስ ዘመን እና ኢትዮጵያ ኤራልድ የሚጠቀሱ ናቸው። በነዚህ ሁለት ነገስታት ወቅት ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦችን የሚያመሳስላቸው ነገረ የህትመቶቹ ይዘት ሲሆን ይህም በአብዛኛው የዘውዱን ስርዓት የሚያሞካሹ መሆናቸው ነበር።

የንጉሳዊ ስርዓት በሀገሪቱ ካበቃ በኃላ ወደ ስልጣን የወጣው የደርግ መንግስት ቀደም ብለው ሲታተሙ የነበሩ የህትመት ውጤቶችን በመዝጋት እና በመውረስ በምትካቸው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እና ሰርቶ አደር የተባሉ ጋዜጦች ታትመው ለስርጭት እንዲቀርቡ አደረገ። በዚህ ስርዓት ምንም አይነት የግል ፕሬስ ያልነበረ ሲሆን በመንግስት ታትመው የሚወጡ የህትመት ውጤቶች በሙሉ የቅድመ ምርመራ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል።

የብሮድካስት አገልግሎትን በተመለከተ የመጀመሪያው ሬድዮ ጣቢያ የተቋቋመው በ1941 ዓ.ም አካባቢ ከጣሊያን ካምፓኒ ጋር በተደረገ ስምምነት ሲሆን ይህ የራድዮ ጣቢያ በጣሊያን ወረራ ወረራ ወቅት ተቋርጦ በ1949 ዓ.ም አካባቢ በድጋሚ የኢትዮጵያ ሬድዮ በሶስት ጣቢያዎች እና በስድስት ቋንቋዎች ስራውን ጀምሯል፡፡በኢትዮጵያ የቴሌቭዥን አገለግሎት በ1960ዎቹ መጀመሪያ የተጀምሯል፡፡

የደርግ ስርዓት ካበቃ በኃላ ወደ ስልጣን የመጣው የሽግግር መንግስቱ ያወጣው የኢትዮጰያ የሽግግር ወቅት ቻርተር በክፍል 1 አንቀፅ (1) (ሀ) ስር የእምነት እና ሀሳብን የመግልፅ መብቶች የተረጋገጡ ሲሆን ከዚህ በኃላ በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የኢፌድሪ ህገ መንግስት ለፕሬስ ነፃነት የተሸለ ሰፋ ያለ ሽፋን በመስጠቱ በርካታ የግል የህትመት ውጤቶች ወደ ኢንደስትሪው ሊገቡ ችለዋል።
በዚህ ጽሁፍ በአሁኑ ወቅት የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው የኢፌድሪ ህገ መንግስት ፣ የሀገሪቱ የህግ አካል የሆኑት ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች እና እነዚህን መሰረት አድርገው የወጡ አዋጆች ፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ የሚያትቱትን እንመለከታለን።

1/ ኢፌዲሪ ህገ መንግስት
በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 ስር ሀሳብን የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት የተረጋጠ ሲሆን ይህ አንቀፅ በዝርዝር ማንኛውም ሰው ሀሳብን በነጻነት የመያዝ እና የመግለፅ መብት እንዳለው፣ የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን በነጻነት እንዲሁም የስነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት የተረጋገጠ መሆኑ፣ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑ፣ ሁሉም ሰው የህዝብ ጥቅምን የሚመለከት መረጃ የማግኘት እድል የተሰጠው መሆኑ እና የመሳሰሉት በህገ መንግስቱ ውስጥ ተካተው የሚገኙ መብቶች የፕሬስ እና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶችን በተሻለ ያረጋገጡ ናቸው። በተጨማሪም ማንም ሰው በማናቸውም ዘዴ ሀሳብን በነፃነት የመሰብሰብት እና የማሰራጨት መብት ተረጋግጦለታል።

ሌላው ከፕሬስ ነፃነት ጋር በተያያዘ የተሰጠው ህገ መንግስታዊ መብት የህዝብ ጥቅምን የሚመለከት መረጃ የማግኘት መብት ሲሆን በተጨማሪም ለነፃው ፕሬስ መረጋገጥ የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ ተከልክሏል። ከእነዚህ መብቶች ጋር በተያያዘ ህገ መንግስቱ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሀሳቦች እና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አስያየቶችን የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ እንደሚደረግለት በመደንገግ በሀገሪቱ የተሻለ የፕሬስ ነፃነት ይሰፍን ዘንድ የህግ ከለላ ለፕሬስ አካሉ መስጠት አንደሚገባ አስቀምጧል።

ሆኖም እነዚህ መብቶች ያለገደብ የሚተገበሩ አይደሉም። ህገ መንግስቱ በአንቀፅ 29/6/ ስር የፕሬስ ነፃነት እና ሀሳብን መግለፅ በመብትነትም ሆነ በነፃነት በማረጋገጥ በኩል ገደብ ሊጣልባቸው የሚችልባቸውን ሁኔታዎች አስቀምጧል። ሀሳብን በነፃነት በመግለፅ በኩል የሚኖር ህገ መንግስታዊ ገደብ በዋናነት የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል በሚወጡ ህጎች ህጎች መሰረት ሊፈፀሙ የሚችሉ ናቸው።

በተጨማሪም በዚሁ አንቅፅ ስር የጦርነት ቅስቀሳዎችን እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች በህግ ሊከለከሉ እንደሚችሉ ተደንግጓል። ይህን በማጠናከር ህገ መንግስቱ የፕሬስ አካሉም ሆነ ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተረዘሩት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን በአንቀፅ 29/7/ ስር ይገልፃል።

በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የፕሬስ እና ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትን በተመለከተ እንዲሁም በእነዚህ መብቶች ላይ ሊጣሉ የሚችሉ ገደቦችን በተመለከተ በአንቀፅ 29 ስር በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም መሰረት ማንኛውም ሰው ከፕሬስ ነፃነት እና መገናኛ ብዙሀን ጋር በተያያዘ የተሰጡ መብቶችን ሲተገብር እነዚህን ህገ መንግስታዊ ገደቦች ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ እና በሀገሪቱ መብቶቹን ለማስፈፀም የሚወጡ ህጎችም ሆነ መመሪያዎች የህገ መንግስቱን መሰረታዊ መርሆዎች የተከተሉ መሆን እንዳለባቸው መረዳት ይቻላል፡፡

2/ አለም አቀፍ ስምምነቶች
ኢትዮጵያ ዋንዮቹን ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ያተኮሩ ዓለም አቀፍ ሰነዶችን ያፀደቀች ከመሆኑም በላይ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 9/4/ ስር እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ የህግ አካል መሆናቸው የተደነገገ ሲሆን በተጨማሪም በአንቀፅ 13/2/ ስር በህገ መንግስቱ የተዘረዘሩት መሰረታዊ መብቶች እና ነፃነቶች ከእነዚህ አለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ መተርጎም እንዳለበት በመደንገግ እውቅና ሰጥታለች። እነዚህ አለም አቀፍ ስምምነቶች ስለ ፕሬስ ነፃነት የሚያትቱትን እንደሚከተለው እንመለከታለን።

ሀ/ የሰብአዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ
ይህ መግለጫ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሀገሮች ላይ ተፈፃሚነት ያለው የሰብአዊ መብት መግለጫ ሲሆን በአንቀፅ 19 ስር “ማንም ሰው አስተያየት የመስጠት ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት እና መብት አለው። ይህ መብት እንያንዳንዱ ሰዉ ያለምንም ተፅህኖ አስተያየት እንዲኖረዉና እና ጠረፍ ሳይወሰነዉ በማናቸዉም ዓይነት መሳሪያ መረጃዎችን ወይም አሳቦችን የመፈለግ የመቀበልና የማስተላለፍ ነፃነትን ይጨምራል” በማለት ሰዎች ነፃ የሆነ ሀሳብን የመግለፅ እና የማስተላለፍ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

ለ/ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለም አቀፍ ቃልኪዳን
ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች መሀከል አንዱ ሲሆን የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ አንቀፅ 19 የሚከተለውን ይደነግጋል፣
1/ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራሱን አስተያየት ሊኖረው መብት አለው፣
2/ ማንኛውም ሰው ሀሳቡን የመግለፅ ነፃነት አለው፣
3/ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 2 ስር የተደነገጉ መብቶች ያጠቃቀም ሁኔታ ልዩ ግዴታዎችን እና ሀላፊነቶችን አብሮ ይዟል። በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ገደቦች ሊደረጉበት ይችላል። ይሁን እንጂ ገደቦቹ በህግ በተደነገጉ እና፡
 

ሀ/ የሌሎች መብቶችንና ክብርን ለማስጠበቅ፣
ለ/ የብሔራዊ ፀጥታን፣ የህዝብን ደህንነት ወይም ጤናን ወይም   ስነምግባርን ለማስከበር መሆን አለባቸው።
ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ከፕሬስ እና መገናኛ ብዙሀን ነፃነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው መብቶች ማለት ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ መረጃን ያለምንም የድንበር ገደብ የመፈለግ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብቶች ለሁሉም ስው የተሰጡ ቢሆንም እነዚህ መብቶች ግን ፍፁማዊ እና ያለምንም ገደብ ሊተገበሩ የሚችሉ አለመሆናቸውን ይልቁንም በህግ በተደነነገ ግዜ የሌሎችን መብት ለማስጠበቅ እና ብሔራዊ ፀጥታን፣ የህዝብ ደህንነት፣ ጤናን ወይም ስነ ምግባርን ለማስከበር መንግስታት በህግ ይህን መብት ሊገድቡ እንደሚችሉ በዚህ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ላይ የተቀመጠ ነው።

ሐ/ የአፍሪካ የሰዎችና የህዝቦች መብቶች ቻርተር
የሰዎች ሀሳብን በነፃ የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ ይህ ቻርተር በአንቀፅ 9 ስር የሚከተለውን አስፍሯል፡
 1/ ማንኛውም ሰው መረጃ የማግኘት መብት አለው
 2/ ማንኛውም ሰው ህግን ተከትሎ ሀሳቡን የመግለፅና የማሰራጨት    መብት አለ።

በዚህም መሰረት ሁሉም ሰው መረጃ የማግኘት፣ ሀሳቡን የመግለፅ እና የማሰራጨት መብት እንዳለው ሲደነግግ ነገር ግን ይህን መብት ለማስፈፀም የሚወጡ ህጎችን መሰረት በማድረግ ሊተገበር የሚገባ መሆኑን የገልፃል።
በአጠቃላይ ከላይ እንደተመለከተው ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው እና የሀገሪቱ የህግ አካል የሆኑ በእነዚህ አለምአቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ የተደነገጉ መብት እና ግዴታዎች በሀገሪቱም ተፈፃሚነት አላቸው። በመሆኑም የፕሬስ ነፃነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት እነዚህ አለም አቀፍ ስምምነቶች ከፍተኛ ሚና ስለሚኖራቸው ታሳቢ ሊደረጉ ይገባል።

4/ የመገናኛ ብዙሀን እና የመረጃ ነጻነትን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 590/2000
ይህ አዋጅ መነሻ ካደረጋቸው በርካታ መሰረታዊ ዓላማዎች መካከል በዜጎች መካከል የሚደረገውን ነጻ የሀሳብ እና የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሀን የአሰራር ነጻነት ላይ መሰናክል የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮችን ማስወገድ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ላይ ታላቅ ሚና መጫወት የሚችል ራሱን በከፍተኛ ስነምግባር እና የሙያ ብቃት ያነጸ ዘርፈ ብዙ የመገናኛ ብዙሀን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ መታመኑ በዋናነት ይገኝበታል፡፡ በተጨማሪም በአዋጁ መግቢያ ላይ ይህ አዋጅ የወጣው የወጣቶችን ደህንነት የሰውን ክብርና መልካም ስም፣ ብሄራዊ ደህንነትን፣ የህዝብን ሰላምና ጸጥታን እንዲሁም ሌሎች ተነጻጻሪ መብቶችና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ሲባል በግልጽ በሚደነገጉ ህጎች ብቻ ሀሳብን በነጻ የመግለጽና በመገናኛ ብዙሀን ነጻነት ላይ ገደቦች እንዲጣሉ የሚያዘውን ህገመንግስታዊ መርህ በማረጋገጥ መሆኑን ተገልጿል፡፡

በዚህ አዋጅ የመገናኛ ብዙሀን ማለት በየጊዜው የሚወጡ የህትመትና ብሮድካስቶችን የሚያካትት የህትመት ስራ እንደሆነ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ ይህ አዋጅ በአብዛኛው ፕሬሱ መረጃን ጠይቆ የማግኘትና ይህ መረጃ ወይም ሀሳብን የመግለጽ መብት እንዴት እንደሚተገበር የሚያተት ነው፡፡

በቅድሚ አንቀጽ 4 የመገናኛ ብዙሀን ነጻነት የሚያብራራ ሲሆን በዚህም የቅድሚያ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑ፤ በመገናኛ ብዙሀን ነጻነት ላይ ገደቦች የሚጣሉት ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ በሚወጡ ህጎች ብቻ መሆኑን እና ማንኛውም የመንግስት አካል የመገናኛ ብዙሀን ማህበራዊ ተግባራቸውን ለመወጣት፡-
ዜና ወይም መረጃን የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት
በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ወይም ትችት የማቅረብ፤
የተለያዩ ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም የህዝብን አስተያየት በመቅረጽ ሂደት የመሳተፍ መብታቸውን ማክበር እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

በተጨማሪም ማንኛውም ኢትዮጲያዊ ዜግነት ያለው ሰው የመገናኛ ብዙሀን ስራ የመስራት መብት እንዳለው እና ጋዜጠኞችም በመረጡት የሙያ ማህበር ራሳቸውን የማደራጀት መብት እንዳላቸው ተገልጿል፡፡ የመገናኛ ብዙሀን ስራ ለመስራት አሳታሚውን ወይም የዜና አገልግሎት ድርጅቱን ስም እና አድራሻ እንዲሁም ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ካሉ አድራሻቸውን የህትመት ስራው ወይም የዜና አገልግሎት ድርጅቱ ስም እና አሳታሚው ወይም በዜና አገልግሎት ድርጅቱ ከሁለት ከመቶ የበለጠ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸውን ሰዎች ስም፣ አድራሻ እና የአክሲዮን ድርሻ መጠናቸውን በመግለጽ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ማግኘት አለባቸው፡፡

ይህ የምዝገባ ሰርተፍኬት ሊሰረዝ የሚችለው የህትመት ወይም የዜና አገልግሎት ድርጅቱ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ስራውን ማቆሙን ካሳወቀ ወይም ድርጅቱ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ባለው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ህትመቱን ማውጣት ያልጀመረ ወይም የዜና አገልግሎት ስራውን ያልጀመረ እንደሆነ መሆኑን አዋጁ ይደነግጋል፡

 መረጃ የማግኘት መብት

የፕሬስ ነጻነት ሀሳብን በፈለጉት መንገድ የመግለጽ/ የማሰራጨት / መብት ጨምሮ መረጃ የማግኘት መብትን እንደሚያካትት በህገመንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ይህ አዋጅም ዜጎች ከማንኛውም መንግስታዊ አካል መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘት እና የማስተላለፍ መብታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ይህን የሚፈልጉትን ማስረጃ በተቻለ ፍጥነት በዝቅተኛ ወጪ ሳይደክሙ የሚያገኙበትን አሰራር ለመመስረት እና የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የአሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግስት አሰራርን ለማጠናከር የሚከተሉት የህግ ድንጋጌዎች ዜጎች መረጃን ጠይቆ የማግኘት መብት እንዳላቸው እና ይህን መብት እንዴት ሊተገበር እንደሚችል ያሳያል፡፡

በአዋጁ በተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በስተቀር ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግስታዊ አካል መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት ያለው ሲሆን ይህን መብት መረጃው በማንኛውም የመንግስት አካል እጅ የሚገኝ መሆን አለመሆኑን የመጠየቅ እና በመንግስት አካሉ እጅ የሚገኘውን ሰነድ የመመልከት፣ ማስታወሻዎችን የመወሰድ፣ ጥቅሶችን የመገልበጥ ወይም ሰነዱ የሚገኝበትን ትክክለኛ ግልባጭ የመውሰድ መብት ያካትታል፡፡

ሆኖም ይህ መረጃን ጠይቆ የማግኘት መብት ያለምንም ገደብ የሚተገበር አይደለም፡፡ በአንቀጽ 15 እንደተገለጸው ይህ መብት በዚህ አዋጅ በተደነገጉ ገደቦች ካልሆነ በቀር ሊገደብ አይችልም፡፡ ይህም ማለት በዚህ አዋጅ መረጃን የማግኘት መብት ሊገደብ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም መረጃ በአስተዳደራዊ ውሳኔ ሚስጥር ነው ተብሎ በመፈረጁ ብቻ በዚህ አዋጅ የተረጋገጠውን መረጃ የማግኘት መብት አፈጻጸምን ሊያስቀር አይችልም፡፡ ስለሆነም በዚህ አዋጅ በግልጽ መረጃው የማይገለጽ መሆኑ ካልተደነገገ በስተቀር በአስተዳደር መስሪያ ቤቶች መረጃው ሚስጥራዊ ነው መባሉ ይህን መረጃ የማግኘት መብትን የሚያሳጣ አይደለም፡፡

ሆኖም በአዋጁ የሚከተሉት የመረጃ ይሰጠኝ ጥያቄዎች ውድቅ ሊደረጉ የሚችሉ መሆናቸው ተደንግጓል፡፡
  የመረጃ ጥያቄው ከሞተ 20 ዓመት ያልሞላውን ሰው ጨምሮ የ3ኛ ወገንን የግል ህይወት በሚመለከት መረጃዎችን ያለበቂ ምክንያት እንዲገለጽ የሚጠይቅ ከሆነ እና ይህ መረጃ ለህዝብ ይፋ ያልተደረገ ወይም የመረጃው ባለቤት እንዲገለጽ ያልፈቀደው ከሆነ፣
  የ3ኛ ወገንን የንግድ መረጃዎች ማለት የንግድ ሚስጥር የ3ኛ ወገን የፋይናንስና የሳይንሳዊ ወይም ቴክኒካል መረጃዎች ሆነው ቢገለጽ 3ኛ ወገን ላይ የፋይናንስ ጉዳት ወይም በንግድ ውድድር ወቅት ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላል ተብሎ የሚገመቱ መረጃዎች ሲሆኑ፣
 

የተጠየቀው መረጃ የመንግስት አካል መገለጽ የሌለበትን መረጃ ልውውጥን በሚመለከት ያደረገውን የውል ግዴታ እንዲያፈርስ የሚያደርግ ከሆነ ወይም 3ኛ ወገን አይገለጽም ብሎ በእምነት የሰጠውን መረጃን የሚመለከት ሆኖ የመረጃው መገለጽ ወደፊት ከተመሳሳይ ምንጭ የሚገኙ ተመሳሳይ መረጃዎች መቀበልን ሊያስተጓጉል የሚችል ከሆነ እና መንግስት እነዚህን መረጃዎች በየጊዜው መቀበል ያለበት ከሆነ፤የተጠየቀው መረጃ የግለሰብን ህይወት ወይም አካላዊ ደህንነት ለጉዳት ሊያጋልጥ የሚችል ከሆነ ማንኛውም አይነት የንብረት መዋቅርን ወይም አሰራር ደህንነትን ሊያሰናክል ይችላል የሚል ምክንያታዊ ግምት ካለ፤የተጠየቀው መረጃ የተፈጸመን ወይም ሊፈጸም የሚችል የህግ ጥሰትን መመርመሪያ፣ መከታተያ፣ መግቻ ወይም መከላከያ ዘዴዎችን ወይም የተግባር መመሪያዎችን የሚመለከት ከሆነ እና የመረጃው መገለጽ ለወንጀል አፈጻጸም ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ውጤታማነታቸውን ሊያሰናክል ወይም ከህግ ማምለጥን ሊያስከትል የሚችል ከሆነ፤

የተጠየቀው መረጃ የሚመለከተው የወንጀል ተጠርጣሪ ክስ ገና ዝግጅት ላይ ያለ ከሆነ ወይም ዝግጅቱ ቢጠናቀቅም ክሱ ገና ያልተጀመረ ከሆነ ወይም ክሱ በመታየት ላይ ያለ ከሆነና የተጠየቀው መረጃ መገለጽ ክሱን ሊያሰናክል የሚችል ከሆነ ወይም የፍርድ ሂደቱን ሚዛናዊነት ወይም ገለልተኝነት ሊያዛባ የሚችል ከሆነ፤የተጠየቀው መረጃ ቢገለጽ ወይም መኖር አለመኖሩ ቢረጋገጥ የሀገሪቱን መከላከያ፣ የሀገር ጸጥታና ደህንነት ወይም አለምአቀፋዊ ግንኙነት ሊጎዳ የሚችል ከሆነ፤የተጠየቀው መረጃ የካቢኔ ሰነዶች ውስጥ የሚገኝ ሆኖ ካቢኔው ለህዝብ ይፋ እንዲሆኑ ከወሰናቸው መረጃዎች ውጪ ሲሆን፤የተጠየቀው መረጃ ቢሰጥ ወይም መኖር አለመኖሩ ቢገለጽ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ወይም የፋይናንስ ደህንነቱን ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችል ከሆነ ወይም መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስተዳደር ያለውን አቅም ሊያዳክም የሚችል ከሆነ፤

የተጠየቀው መረጃ የመንግስት አካላትን የንግድ ሚስጥሮችን የያዘ ከሆነ ወይም የንግድ ሚስጥር ባይሆንም የማንኛውም መንግስት አካል ጥቅም ሊጎዳ የሚችል የፋይናንስ፣ የንግድ ወይም የቴክኒክ ወይም የሳይንስ መረጃ የያዘ ከሆነ እና መገለጹ ማንኛውንም የመንግስት አካል የሚያደርገውን የንግድ ውድድር ሊጎዳ ይችላል ወይም በሚያደርጋቸው ውሎች እና ድርድሮች ተጠቃሚ እንዳይሆን ሊያደርግ ይችላል የሚል ምክንያታዊ ግምት ካለ፤
  የተጠየቀው መረጃ የመንግስት የስራ ሰነዶች ሆነው በተለይም ፖሊሲ ለመቅረጽ በህግ የተሰጠ የስራ ሀላፊነት ለመወጣት የተደረገ ውይይት በሆነ እና መገለጹ የፖሊሲውን ስኬታማነት ሊያስቀር ይችላል የሚል ምክንያታዊ ግምት ካለ፤ በተጨማሪም መረጃው የመንግስት አካላት የሚጠቀሙባቸው የቁጥጥር፣ የኦዲት፣ የምርመራ እና የመሳሰሉ የውስጥ አሰራሮችን እና መመሪያዎችን የያዘ ከሆነ እና ቢገለጽ የምርመራ ወይም የኦዲት አሰራሮችን ውጤታማነት ሊያስተጓጉል የሚችል ከሆነ፤

በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩ ምክንያቶች በአዋጁ በይበልጥ በዝርዝር የተቀመጡ ሲሆን የመንግስት አካላት እነዚህን የአዋጁን ድንጋጌዎች መሰረት በማድረግ ካልሆነ በስተቀር የማንንም ሰው መረጃን የማግኘት መብት ሊገድቡ አይችሉም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በአዋጅ የተደነገገው መብት በተለይ 3ኛ ወገንን የሚመለከቱ መረጃዎች / እነዚህ የግልም ሆነ የንግድ መረጃዎችን ይጨምራል/ አስቀድሞ ለህዝቡ ይፋ ተደርገው ከሆነ፣ የመረጃው ባለቤት መረጃውን እንዲሰጥ በጽሁፍ የፈቀደ እንደሆነ እና የመረጃው መገለጽ በህዝብ ደህንነት ወይም በአካባቢ ደህንነት ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋን ለማሳወቅ አስፈላጊ ከሆነ የተጠየቀውን መረጃ መከልከል አይቻልም፡፡

ማንኛውም የተጠየቀ መረጃን በመስጠት ሂደት ውስጥ በመረጃው መገለጽ ጥበቃ በተደረገላቸው ጥቅሞች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በመረጃው መገለጽ ሊገኝ ከሚችለው የህዝብ ጥቅም የሚበልጥ መሆን አለመሆኑ መመዘን ያለበት መሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ ይህም ማለት የመረጃው መገለጽ ወይም የመረጃ ጥያቄው ተቀባይነት ማግኘቱ ይህ ጥያቄ ውድቅ ቢደረግ ከሚገኘው የህዝብ ጥቅም የሚበልጥ ካልሆነ በስተቀር ጥያቄው ውድቅ መደረግ የለበትም፡፡ ስለሆነም መረጃ የማግኘት መብት በመከልከል ሂደት ውስጥ ሁሌም የህዝብ ጥቅም ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡

ሌላው መረጃ ጠይቆ ይህ ጥያቄ በህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ውድቅ የተደረገበት ሰው እና በዚህ ቅሬታ ያለው ሰው ቅሬታውን ማቅረብ ስለሚችልበት አሰራር በአዋጁ የተቀመጠ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በህዝብ ግንኙነቱ ሃላፊ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ማንኛውም ሰው ውሳኔው ከተሰጠ ጀምሮ ባሉት 30 ቀናት ለመንግስታዊ አካሉ የበላይ ሃላፊ ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህ አቤቱታ የቀረበለት የመንግስት የበላይ አካል በ10 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡ በዚህ የመንግስት አካሉ የበላይ ሃላፊ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ሰው ይህን አቤቱታ በ30 ቀናት ውስጥ ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ይግባኝ ማቅረብ ይችላል፡፡

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምም መረጃው መገለጽ የሌለበት መሆኑን ለማረጋገጥ ሰርተፊኬት ከተሰጠባቸው ሰነዶች በስተቀር በመንግስት አካላት እጅ የሚገኙ ማንኛውም ሰነዶችን አስቀርቦ በመመርመር ይግባኙ በቀረበበት በ30 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡ በዚህ በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋሙ ውሳኔ ቅር የተሰኘ ሰው መረጃው የፌደራል የመንግስት አካልን የሚመለከት ከሆነ ለፌደራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት መረጃው የክልል የመንግስት አካልን የሚመለከት ከሆነ ለክልል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኙን በ30 ቀናት ውስጥ ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህ ይግባኝ የቀረበለትም ፍ/ቤት አስፈላጊውን ሰነድ አስቀርቦ በመመርመር በቀረበለት ይግባኝ ላይ በሰላሳ ቀን ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡

ማንኛውም ሰው ሀላፊነቶችና ግዴታዎችን በቅን ልቦና ለመፈጸም ከተረገደ ድርጊት ውጪ በዚህ አዋጅ የተረጋገጡትን መረጃ የማግኘት መብቶች ለመጣስ በማሰብ ሆን ብሎ ማንኛውም ሰነድ ያጠፋ፣ ያበላሸ፣ የቀየረ ወይም የደለዘ፣ የደበቀ፣ በተንኮል የከለከለ፣ ያፋለሰ ወይም ሀሰተኛ ሰነድ የሰራ እንደሆነ የወንጀል ጥፋቱ በፍርድ ሲረጋገጥበት በገንዘብ ወይም ከሁለት አመት በማይበልጥ እስራትእንደሚቀጣ አዋጁ ይደነግጋል፡፡

ሌላው የመገናኛ ብዙሀን መብቶችና ግዴታዎች ጋር ተያይዞ በአዋጁ አንቀጽ 40 ስር በመገናኛ ብዙሀን ቢቀረበ የፍሬ ነገር ዘገባ መልካም ስሙና ክብሩ የተጎዳበት ማንኛውም ሰው ዘገባው በቀረበበት መገናኛ ብዙሀን ላይ ያለክፍያ መልስ የመስጠት መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡ ይህ መልስ የመስጠት መብቱ የተነፈገ ማንኛውም ሰው የህትመቱ ወይም የፕሮግራሙ አዘጋጅ ተገዶ መልሱን እንዲያወጣለት ለፍ/ቤት አቤቱታውን ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን ፍ/ቤቱ አቤቱታ ተቀብሎ በ10 ቀናት ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡


 የእገዳ እርምጃዎችን ስለመውሰድ
አዋጁ በየጊዜው የሚወጣ ህትመት ወይም መጽሀፍ ሊታገድ የሚችልባቸው ሁኔታዎች ያስቀመጠ ሲሆን በዚህ ህግ ከተደነገገው ውጪ ይህ እገዳ ሊፈጸም አይችልም፡፡
የፌዴራል ወይም የክልል ዐቃቤ ህግ በብሄራዊ ደህንነት ላይ ከስርጭት በኋላ በማስቀጣት ሊቀለበስ የማይችል ግልጽና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል በየጊዜው የሚወጣ ህገወጥ ህትመት ወይም መጽሀፍ ሊሰራጭ መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ሲኖረው የህትመት ውጤቱ እንዳይሰራጭ ፍ/ቤት እንዲያዝ ማመልከት ይችላል፡፡ ሆኖም ዐቃቤ ህግ ከነገሩ አጣዳፊነት የተነሳ ጉዳቱን ለመከላከል የፍ/ቤት የማገጃ ትዕዛዝ ማግኘት ባልቻለ ጊዜ የህትመት ውጤቱን ወይም መጽሀፉ እንዲታገድ ትዕዛዝ መስጠት ይችላል፡፡
ዐቃቤ ህግ ትዕዛዝ ሲሰጥ ትዕዛዝ በተሰጠ በ48 ሰዓት ውስጥ ለፍ/ቤት ማስታወቅ ያለበት ሲሆን ፍ/ቤቱም በ24 ሰዓት ውስጥ የእገዳ እርምጃውን የሚያጸድቅ መሆን አለመሆኑን ማስታወቅ አለበት፡፡ በዚህም መሰረት ፍ/ቤቱ በዐ/ህግ የተሰጠው ትዕዛዝ ሲቀርብለት ተመልክቶ የሚከተለውን ይወስናል፡፡

1/ የህትመት ስራው ወይም መጽሀፉ ህገ-ወጥና ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሆኖ ካገኘው የዐ/ህጉን ትዕዛዝ በማጽደቅ ዐቃቤ ህጉ የማገድ እርምጃውን ከወሰደበት ጊዜ ጀምሮ ባለው የሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ክሱን እንዲመሰርት ወይም ህትመቱ እንዲወረስ ማመልከቻ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ዐ/ህግ ይህ ትዕዛዝ ካልፈጸሙ የህትመት ስራው ወይም የመጽሀፉ ስርጭት እንዲቋረጥ ዐ/ህግ የሰጠው ትዕዛዝ ይነሳል፡፡

2/ የህትመት ስራው ወይም መጽሀፉ ህግን የማይተላለፍና ከፍተኛ ጉዳትን የማያስከትል ሆኖ ካገኘው በዐ/ህጉ የተሰጠውን የእገዳ ትዕዛዝ ውድቅ በማድረግ የታገደው ህትመት እንዲለቀቅ ትዕዛዝ መስጠት አለበት፡፡
ሌላው በአዋጁ የተቀመጠው የአዋጁን ድንጋጌዎች መተላለፍ ስለሚያስከትሉት ቅጣት ነው፡፡

እነዚህ ቅጣቶች ተፈጻሚ የሚሆኑት በአዋጁ ላይ የተቀመጡ ግዴታዎችን ሳያሟላ የቀረ ሰው ላይ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በአዋጁ ላይ በአንቀጽ 7 የመገናኛ ብዙሀን ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የወጣውን ቅድመ ሁኔታ የተላለፈ፣ የመገናኛ ብዙሀን ድርጅቱ በአንቀጽ 6/2/ እንደተቀመጠው የህግ ችሎታ ያለው ሃላፊ ወይም ዋና አዘጋጅ ካልሰየመ፣ በአንቀጽ 9/6/ ስር በተገለጸው አግባብ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ላይ የሚሰፍር የአሳታሚ ወይም የዜና አገልግሎት ድርጅቱ መረጃዎች ላይ የተደረገ ለውጥን አለማስታወቅ፣ በአንቀጽ 10 መሰረት በህትመት ላይ ስለሚገለጹ ነገሮች ያለ ክፍያ ስለሚሰጡ ቅጂዎች የተደነገገውን መተላለፍና በአንቀጽ 40 መሰረት በህትመት ላይ እንዲወጣ የተላኩ መልስ ወይም ማስተካከያዎችን አለማውወጣት የሚሉ የአዋጁ ድንጋጌዎችን የተላለፈ በአዋጁ መሰረት በፍ/ቤት ቅጣት ሊጣልበት ይችላል፡፡

በዚህም መሰረት የተለያዩ የአዋጁን ድንጋጌዎች የተላለፈ ማንኛውም ሰው በፍ/ቤት እስከ ብር 20000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሀን ውጤቱ እንዳይሰራጭ ሊታገድ ይችላል፡፡
ይርጋን በተመለከተ የአዋጁን ድንጋጌዎች በመተላለፍ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ህትመቶቹ ከተሰራጩበት ወይም ከተላለፉበት ቀን አንስቶ እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ክሶቹ ካልቀረቡ በይርጋ ቀሪ ይሆናሉ፡፡ በብሮድካስት ለሚፈጸም ጥፋት ጥፋቱ የተፈጸመበት ፕሮግራም ከተላለፈበት ቀን ጀምሮ ባለው ስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የወንጀል ክስ ካልተመሰረተ ክሱ በይርጋ ቀሪ ይሆናል፡፡

4/ በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ህግ
የወንጀል ህጉ ሀሳብን ከመግለፅ ነፃነት ጋር በተያያዘ ስለሚፈፀሙ ወንጀሎች የሚኖረውን አላፊነት በተመለከተ ከአንቀፅ 42-47 ባሉት አንቀፆች የተደነገገ ሲሆን በአንቀጽ 42(1) ላይ እነዚህ ድንጋጌዎች የተቀመጡት ሀሳብን የመግለፅ ነፃነትን ለመጠበቅና ይህም ነፃነት ከመጠን እንዳያልፍ ለማገድ መሆኑ ተገልፃል።

በመገናኛ ብዙሀን አማካይነት የሚደረጉ ወንጀሎች በጋዜጦች፣ በመፃህፍት፣ በበራሪ ፅሁፎች፣ በመጽሔቶች፣ በሚለጠፉ ወረቀቶች፣ በስዕሎች፣ በሲኒማ፣ በሬድዮ ወይም በቴሌቭዥን ስርጭት ወይም በማናቸውም ሌላ የህዝብ መገናኛ በሆነ ዘዴ ሚፈፀሙ ናቸው። ስለሆነም በእነዚህ ዘዴዎች የሰውን ክብር መንካት ወይም የግልን ወይም የጋራ ደህንነትን በማደፍረስና በወንጀል ህጉ ተከብሮ የሚኖር ማናችውንም ህጋዊ መብት መንካት በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ተብለው ይፈረጃሉ።
በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ያለው አላፊነት።

በወንጀል ህጉ በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ያለው አላፊነትን በተመለከተ እንደህትመት ውጤቱ አይነት አንደሚከተለው ተዘርዝሯል፣
1/ በየግዜው የሚወጣ ህትመት ከሆነ ፣ በዚህ አይነት የህትመት ውጤት ለተፈፀመ ወንጀልን በተመልከት ሀላፊነት የሚወስደው፡
• የፕሬስ ውጤቱ ሲታተም በዋና አዘጋጅነት የተመዘገበው ሰው፣
• ፕሬሱ ፍቃድ የሌለው ከሆነ ወይም ሀላፊ የሆነው ዋና አዘጋጅ ብቁ ካልሆነ ወይም ዋና አዘጋጁ በስልጣኑ መገልገል እንደማይችል በግልፅ የሚመለከቱ ሁኔታዎች ካሉ ወይም ስልጣኑ የይስሙላ ከሆነ ወይም ስራውን ከተወ ፕሬሱ አሳታሚ ሀላፊነት ይወስዳል፣
• የፕሬስ ውጤቱ በተሰራጨበት ወቅት የፕሬሱን አሳታሚ ለማወቅ ካልተቻለ በአሳታሚው ምትክ አታሚው ሀላፊ ይሆናል፣
• የአታሚው ማንነት ባልታወቀ ግዜ ውጤቱን ያሰራጨው ማንኛውም ሰው ሀላፊ ይሆናል
በተጨማሪም ከሀገር ውጭ የታተመ ህትመትን በሚመለከት ሀላፊ የሚሆነው በውጤቱ በግል ለመጠቀም ከሚያስገባው ሰው ውጭ የሆነ አስመጪ ወይም የፕሬስ ውጤቱን ያሰራጨው ሰው ሀላፊ ይሆናል።

2/ የፕሬስ ውጤቱ በየግዜው ከሚወጣ ህትመት ውጭ ከሆነ
በእነዚህ የህትመት ውጤቶች አማካኝነት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ሀላፊነቱን የሚወስደው፡
• የደራሲው ስም በህትመት ውጤቱ ላይ ከተገለፀ ደራሲው ሀላፊ ይሆናል።ሆኖም የህትመት ውጤቱ የተሰራጨው ከደራሲው ፍቃድ ውጪ ከሆነ ስሙ፣ የብህር ስሙ ወይም እውነተኛ ያልሆነ ሰሙ በፕሬስ ውጤቱ ላይ የተገለፀው ከፍቃዱ ውጪ መሆኑ ከተረጋገጠ ደራሲው ሃላፊ አይሆንም፡፡

• የህትመት ውጤቱን ከአንድ በላይ ደራሲዎች የያዘ በመሆኑ ደራሲው ሀላፊ መሆን ካልቻለ እና በህግ መሰረት የህትመቱ ዋና አዘጋጅ ከተሾመ ይህ ዋና አዘጋጅ ሀላፊ ይሆናል፣
• ህትመቱ ታትሞ በወጣበት ግዜ ደራሲው በህይወት የሌለ ከሆነ አዘጋጁ ሀላፊ ይሆናል። ሆኖም የአዘጋጁ ስም፣ የብህር ስሙ ወይም እውነተኛ ያልሆነ ስሙ ከአዘጋጁ ፍቃድ ውጪ በፕሬስ ውጤቱ ላይ መታተሙ ከተረጋገጠ አዘጋጁ ሀላፊነት አይወስድም፡፡
• የወንጀል ድርጊት ለተፈፀመበት የፕሬስ ህትመትና ስርጭት ደራሲው ወይም አዘጋጁ ሀላፊ ካልሆነ ወይም በሞት ከተለየ አሳታሚው ሀላፊ ይሆናል።የአሳታሚው ማንነት ካልተረጋገጠ ወይም ከሌለ አታሚው ሀላፊ ይሆናል።

ለዚህ የህግ ድንጋጌ አላማ በየግዜው ከሚወጣ የህትመት ውጤት ውጪ ለሆኑ የፕሬስ ስራዎች አዘጋጅ የሚባለው የህትመቱ ደራሲ ባይሆንም ህትመቱ እንዲታተምና እንዲሰራጭ ያደረገ ማንኛውም ሰው ሲሆን አሳታሚ ደግሞ የሌሎችን የህትመት ስራዎች እየተቀበለ ለህትመት ለስርጭት ለማብቃት የሚሰራ ሰው ማለት ነው።
3/ የመገናኛ ብዙሀን ውጤቱ በሬድዮ ወይም በቴሌቪዥን ወይም ይህን በመሳሰሉ የመገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጭ ሲሆን የፕሮግራሙ ሀላፊ እሱ ከሌለ ደግሞ ባለፍቃዱ ሀላፊ ይሆናል።

ሌላው ከወንጀል ሀላፊነት ጋር በተያያዘ  የጦር መሳሪያ ይዞ በማመፅ ወይም የእርስ በእርስ ጦርነትን በማነሳሳት በመንግስት ላይ በሚደረግ ወንጀል፣ በክዳት፣ በስለላ፣ለወንጀል ድርጊት በማነሳሳትና በአባሪነት፣ በሰብአዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ ወታደራዊ ትዕዛዞች እንዲጣሱ በማድረግ፣ ሌላውን ሰው በማነሳሳት፣ ወታደራዊና መንግስታዊ ሚስጥርን በመግለፅ፣ የሀሰት ወሬችን ነዝቶ ህዝብን በማነሳሳት ወይም በህግ የታዘዘን ሚስጥር የመጠበቅ ሀላፊነትን ሆን ብሎ በመተላለፍ በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት ወንጀሎች ተፈፅመው ከሆነ በደራሲነት፣ በአመንጪነት ወይም በሳታሚነት በመሳተፍ የወንጀሉ ተካፋይ የሆነ ሰው በወንጀል ተጠያቂ ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በተመለከተ ሀላፊነት የሚወስዱት እንደመገናኛ ብዙሀኑ የስርጭት መንገድ ከላይ በተዘረዘረው መሰረት የሚገኙ ሰዎች ሲሆኑ በመጀመሪያ ደረጃ ሀላፊ የሚሆነው ሰው በሀገር ውስጥ የመኖርያ አድራሻው ካልታወቀ ወይም የመኖሪያ አድራሻውን ለማረጋገጥ ካልተቻለ ከእርሱ ቀጥሎ የተመለከተው ሰው በሀላፊነት እንደሚጠየቅ የወንጀል ህጉ የደነግጋል።
ሌላው በወንጀል ህጉ ከፕሬስ ነፃነት ጋር በተያያዘ የተደነገገው የመረጃ ምንጭን በሚስጥር የመጠበቅ መብት ሲሆን በዚህም መሰረት የማንኛውም የፕሬስ ህትመት አሳታሚ ወይም አዘጋጅ የደራሲውን ስም ወይም የብዕር ስም በፕሬስ ውጤቱ ላይ እንዲገልፅ ማስገደድ እንደማይቻል እና ማንኛውም የፕሬስ አሳታሚ ወይም አዘጋጁ የተጠቀመበትን የዜና ወይም የመረጃ  ምንጭ እንዲገልፅ እንደማይገደድ  ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ይህ መብት ለመገናኛ ብዙሀን የተሰጠ ቢሆንም በወንጀል ህጉ ህገ መንግስታዊ አስተዳደር፣ የሀገር መከላከያ ሀይልን፣ የመንግስት ፀጥታና ብሔራዊ ደህንነትን ለመጠበቅ የወጡ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ የተፈጸሙ ወንጀሎችን በሚመለከት ግልፅ እና የቅርብ ግዜ አደጋን የሚያስከትል ሲሆን ወይም ከባድ ወንጀል ሲያጋጥምና የመረጃ ምንጩን ማወቅ አማራጭ የሌለውና ወሳኝ ሆኖ ሲገኝ የፕሬስ አሳታሚው ወይም አዘጋጁ የመረጃ ምንጩን እንዲገልፅ በፍርድ ቤት ሊታዘዝ ይችላል፡፡

በአጠቃላይ የወንጀል ህጉ በመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት ወንጀሎች ተፈፅመው ቢገኙ ተጠያቂነት የሚሆነውን አካል ከላይ በዝርዝር እንደተቀመጠው የለየ ሲሆን ይህም ሰዎች የህትመት ውጤቶችን በማንኛውም መልኩ ለህዝቡ ሲያቀርቡ የሰውን ክብር፣ የህገ መንግስቱን እና የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ መሆን እንዳለበት እና ይህ ሳይሆን ቢቀር እና በአዘጋጁ ፣ በአስታሚው ወይም በደራሲው አማካኝነት ለህዝብ የተሰራጨ የህትመት ውጤቶች የሌላ ሰውን መብት የሚጋፉ ወይም የወንጀል ህጉን ድንጋጌዎች ተላልፈው ቢገኙ ለእነዚህ ህትመቶች መሰራጨት ሀላፊነት የወሰዱ ወይም በማሰራጨት ሂደቱ የተካፈሉ ግለሰቦች በወንጀል ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያስገነዝብ ነው፡፡

5/ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999
ይህ አዋጅ መሰረት ካደረጋቸው አላማዎች ውስጥ የብሮድካስት አገልግሎት በህገ መንግስቱ የተረጋገጡ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ፣ መረጃ የማግኘት የመምረጥ የመመረጥና የመሳሰሉትን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወቱ እና እነዚህን አገልግሎቶች በአግባቡ እና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ እና የብሮድካስት አገልግሎት በመስጠት ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎን መብት እና ግዴታ በግልፅ መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በአዋጁ ብሮድካስት አገልግሎት ማለት ህዝብን ለማስተማር፣ ለማሳወቅ ወይም ለማዝናናት የሚከናወን የሬድዮ ወይም የቴሌቭዥን ስርጭት አገልግሎት ነው፡፡ የብሮድካስት ባለስልጣን ራሱን የቻለ የፌደራል መስሪያ ቤት ሆኖ በዚህ አዋጅ የተቋቋመ ሲሆን አላማውም ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጾ የሚያደርግ ጥራቱን የጠበቀ፣ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ የብሮድካስት አገልግሎት እንዲስፋፋ ማድረግ እና መቆጣጣጠር ነው፡፡ የብሮድካስት ባለስልጣን ለብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ ይሰጣል፣ ይሰርዛል ወይም የማገድ እና ሌሎች በአዋጁ በዝርዝር የተቀመጠውን ስልጣን እና አላፊነቶች ይወጣል፡፡

የብሮድካስት አገልግሎት ዓይነቶች በሶስት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም
1. የመንግስት የብሮድካስት አገልግሎት
2. የንግድ የብሮድካስት አገልግት
3. የማህበረሰብ የብሮድካስት አገልግሎት ናቸው፡፤
ማንኛውም ሰው ከባለስልጣኑ የብሮድካስት ፍቃድ ሳይሰጠው በብሮድካስት አገልግሎት ስራ ላይ መሰማራት የማይችል ሲሆን ባለስልጣኑም በአዋጅ የተቀመጡትን መመዘኛዎች መሰረት በማድረግ ለቀረበለት ማመልከቻ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

ሀሳብን ወይም መረጃን በፈለጉት መንገድ ማሰራጨት በህገመንግስቱ የተሰጠ መብት ሲሆን ይህን መብት በብሮድካስት አገልግሎት ዘርፍ የሚተገበርበትን መንገድ አዋጁ እንደሚከተለው አስቀምጧል፡፡ ማንኛውም የብሮድካስት አገልግሎት ፍቃድ ያለው ሰው ለስርጭት የሚያቀርበው ፕሮግራም የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያንጸባርቅና ሚዛናዊ መሆን አለበት በተጨማሪም ፕሮግራሙ ይዘቱና ምንጩ ትክክለኛ የሆነ ከአድልኦ የጸዳ፣ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መሆን ያለበት ሲሆን በብሮድካስት አገልግሎት የሚቀርቡ ፕሮግራሞች የሚከተሉት ይዘቶች ሊኖራቸው አይገባም፡፡

• የሰው ልጆችን ስብዕና እና ነጻነት ወይም ስነምግባርን የሚጻረር ወይም የሌሎችን እምነት የሚያንኳስስ፤
• በመንግስት ጸጥታ ወይም በህገመንግስቱ መሰረት የተቋቋመው የመንግስት አስተዳደር ወይም በሀገር መከላከያ ሀይል ላይ የወንጀል ድርጊት የሚፈጽም፤
• የግለሰብን፣ የብሄር ብሄረሰብን፣ የህዝብን ወይም የድርጅትን ስም የሚያጠፋ ወይም በሀሰት የሚወነጅል፣
• ብሔረሰብን ከብሄረሰብ የሚያጋጭ ወይም በህዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግጭትን የሚያነሳሳ፤
• ጦርነት የሚቀሰቅስ ይዘት ያላቸውን ፕሮግራሞች ማስተላለፍ አይቻልም፡፡

በመሆኑም በብሮድካስት አገልግሎት የሚሰራጩ ፕሮግራሞች የሰውን ክብርና ስብእና ያከበሩ የሀገሪቱን ጸጥታና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ የተዘጋጁና መቻቻልን የሚሰብኩ መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም የልጆችን አመለካከት፣ ስሜትና አስተሳሰብ ሊጎዱ የሚችሉና ወደአልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያዘነብሉ የሚገፋፉ የብሮድካስት ስርጭቶች ልጆች ሊመለከቱ እና ሊያዳምጡ በሚችሉበት ሰዓት ማስተላለፍ በአዋጁ የተከለከለ ነው፡፡

 የሰውን ሰብዓዊ ክብር ከመጠበቅ አንጻር ማንኛውም የብሮድካስት አገልግሎት ባስተላለፈው ፕሮግራም መብቴ ተነክቷል ወይም በአግባቡ አልቀረበም ለሚል ሰው ስለጉዳዩ መልስ ለመስጠት ያለውን መብት ማክበርና የሚሰጠውን መልስ በተመሳሳይ ጊዜ በግልጽ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት፡፡

በመጨረሻም ማንኛውም ሰው በአዋጁ የተቀመጡ ግዴታዎችን ተላልፎ የተገኘ እንደሆነ በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ወይም ከብር 5000 እስከ 50000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ የተደነገገ ሲሆን ከእነዚህ ጥፋቶች መካከል፤
• ፍቃድ ሳይኖር የብሮድካስት አገልግሎት መስጠት፤
• አዋጁ ለስርጭት የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ይዘት ሊሆን አይገቡም ብሎ የደነገጋቸውን ድንጋጌዎች መተላለፍ፤
• የልጆችን ስሜት አመለካከትና አስተሳሰብ የሚጎዳ ፕሮግራም ማሰራጨትና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

በአጠቃላይ ይህ የብሮድካስት አዋጅ ትኩረት ያደረገው ሰዎች ሀሳባቸውን በሬድዮም ሆነ በቴሌቪዥን የሚገልጹበትን መንገድ ማሳየት ወይም ይህ መብት የሚተገበርበትን መንገድ መደንገግ ላይ ሲሆን በዚህም የብሮድካስት ባለስልጣን ተቋቁሞ ማንኛውም ሰው በብሮድካስት አገልግሎት ዘርፍ መሰማራት ከፈለገ በአዋጁ የተቀመጡ መስፈርቶችን በሟሟላት ፍቃድ ማግኘት እንደሚችልና በዚህ ፍቃድ መሰረት የማህበረሰቡን የባህል እሴቶች፣ የህዝቦችን መቻቻል፣ የሰውን ሰብዓዊ ክብር፣ የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ እና ህገመንግስታዊ ስርአቱን የሚያከብሩ ፕሮግራሞችን ማስተላለፍ እንደሚችል ይህ ካልሆነ እና ሰላምና ጸጥታን የሚያደፈርሱ የህዝቦችን ተከባብሮ መኖር ሳይሆን የእርስበእርስ ግጭትን የሚያነሳሱ፣ ጦርነት የሚቀሰቅሱ እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ ፕሮግራሞችን የሚያሰራጩ ከሆነ ቅጣት ሊጣል እንደሚችል አዋጁ ይደነግጋል፡፡

ማጠቃለያ
በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ካገኙ ሰብአዊ መብቶች መካከል ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አንዱ ሲሆን ይህን መብት ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡ በአገራችንም ሀሳብን የመግለፅ መብት ሕገ መንግስታዊ ዋስትና ያገኘ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ይህ መብት እንዴት ይተገበራል የሚለውን ለመመለስ የተለያዩ አዋጆች ተቀርፀው ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ እዚህ ጋር ታሳቢ መደረግ ያለበት ማንኛውም መብት ከራሱ ጋር ይዞ የሚመጣው ግዴታ እንደመኖሩ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትም ህገ መንግስታዊ ግዴታዎች አሉት፡፡

ስለሆነም ማንኛውም ሰው መብቱን በመተግበር ሂደት የሰዎችን ሰብአዊ መብት ማክበር፣ የሀገሪቱን ሰላም ደህንነት መጠበቅ  እና የወጣቶችን ደህንት መጠበቅ እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡ በተጨማሪም ይህ መብት በጠንካራ መልኩ ይተገበር ዘንድ በአገሪቱ ውስጥ ጠንካራ፣ አስተማማኝ፣ በሙያ ስነ ምግባር የዳበረና የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በሙሉ አቅሙ መግለፅ የሚችል የግል ፕሬስ መኖር አለበት፡፡

ሆኖም ከፕሬስ  እና መገናኛ ብዙሀን ነፃነት  ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የፕሬስ ጉዞ አንድ ክፍለ ዘመን ያህል ያስቆጠረ ቢሆንም የግሉ ፕሬስ ስራ ላይ ከዋለ ግን ገና ሁለት አስርት አመታትን ያስቆጠረ ነው በመሆኑ የልምድ ማነስ እና በህብረተሰባችን ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን አንፃር መረጃን ሙያዊ ስነ ምግባር ተላብሰው ከሚያቀርቡ የፕሬስ አካላት ይልቅ ለፕሮፓጋንዳ እና ቅስቀሳ ይዘት ላላቸው የፕሬስ ውጤቶች ትኩረት መስጠቱ ፕሬስ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን እንዳይጠቁም፣ ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብቶች መከበር እንቅፋት የሚሆኑ ምክንያቶች በአግባቡ እንዳይጠቁም እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የራሱን አስተዋፅሆ እንዳያደርግ እንቅፋት እየፈጠረ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግስትም የፕሬስ ነፃነትን የሚመለከቱ የህግ ማህቀፎችን ከመዘርጋት ባሻገር የፕሬስ አካሉ የተሟላ ሙያዊ ስነ ምግባር ያለው፣ በተገቢው መያዊ እውቀት እና ክህሎት የተደራጀ በመሆን በአገሪቱ የእድገት ጉዞ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችል ይሆን ዘንድ የተስፋፋ የትምርት እና ስልጠና በመስጠት ብቁ የፕሬስ አካል ለመገንባት የበኩሉን ጥረት ማድረግ አለበት፡፡

ዋቢ ሰነዶች
1. የኢፌድሪ ሕገ መንግስት
2. ሰብአዊ መብቶችን የሚመለከቱ አለምአቀፍ ሰነዶች……… በኢ.ፌ.ድ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴር እና በኖርዌይ መንግስት ትብብር የተዘጋጀ
3. የመገናኛ ብዙሀንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000
4. የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999
5. በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ህግ
6. The legal framework for freedom of expression in Ethiopia………..by Daniel Bekele
7. Media in Ethiopia: The beginning,development and challenges……by Tdeesse Zinaye
8. Mizan Law Review “freedom of expression in Ethiopia: the jurisprudential Dearth”……. By Gedion Timothewos